የተከበራችሁ ባለአክሲዮኖች፣

የተከበራችሁ የዲሪክተሮች ቦርድ አባላት፣

ክቡራትና ክቡራን!

ጥሪያችንን አክብራችሁ በባንካችን አሥራ ስምንተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመካፈል ስለተገኛችሁ በዲሪክተሮች ቦርድ አባላት፣ በባንኩ ሥራ አመራር አካልና በራሴም ስም እያመሰገንኩ ሁላችሁንም እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡

እ.ኤ.አ. ሰኔ 30 ቀን 2016 የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በአገሪቱ የሚገኙ ባንኮችን በብርቱ የፈተነ ወቅት ነበር፡፡ በዓለም የሸቀጥ ግብይት ላይ በታየው መቀዛቀዝና በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ባላቸው ሚና በቁንጮነት ደረጃ በሚቀመጡ የበለፀጉ አገራት ላይ በታየው አጠቃላይ አለመረጋጋት እንዲሁም በአገር ውስጥ በወጪ ንግድ ዘርፍ በታየው ደካማ ክንውንና ይህንን ተከትሎ በታየው ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ በበጀት ዓመቱ የሥራ እንቅስቃሴያችን ላይ የተፈጠሩ ጫናዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጎልተው ታይተዋል፡፡

 

ይሁንና ይህንን መሠል ተግዳሮቶች ተደቅነውበትም እንኳን ሕብረት ባንክ አ.ማ.  ተደራሽነቱን በማስፋት ማህበረሰባችን የባንክ አገልግሎትን በብዙ አማራጭ ማግኘት እንዲችል እንዲሁም የባንካችንን አገልግሎት ሁሉን አቀፍ ወይም አካታች እንዲሆን ውጤታማ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ በተቀማጭ ገንዘብና በብድር በሴክተሩ ያለንን የገበያ ድርሻ በማሳደግ ረገድም ብርቱ ጥረት በማድረግ ስኬታማ ለመሆን ችሏል፡፡

 

ክቡራትና ክቡራን !

 

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ባንኩ ዓላማ አድርጎ የያዛቸውን መንታ ግቦች ማለትም አገልግሎቶቹን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለደንበኞቹ ማቅረብ እንዲሁም የባንኩን የተቀማጭ ገንዘብ በማሳደግ የብድር አገልግሎት አቅሙን ማጠናከር፤ ከዳር ለማድረስ በቅርንጫፍ ማስፋፋት እንዲሁም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ የባንክ አገልግሎቶችንና አዳዲስ የአሰራር ዘዴዎችን በመቀየስ ረገድ ጠንካራ ሥራ ሠርቷል፡፡ በዚህም የባንኩ ቅርንጫፎች በበጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ላይ 161 ሲደርሱ የባንኩ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ ብር 13.63 ቢሊዮን በመሆን ከግል ባንኮች ጋር በንፅፅር ሲመዘን የ4ኛ ደረጃ ሊይዝ ችሏል፡፡ በዚህ ረገድ የተመዘገበው ውጤት እጅግ በጣም ጥሩ የሚባል ሲሆን፤ እ.ኤ.አ. ሰኔ 30 ቀን 2015 በባንኩ ከነበረው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ጋር ሲወዳደር የ16.2 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

በብድር እንቅስቃሴ ረገድም ባንኩ በበጀት ዓመቱ ለአገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋፅኦ እያደረጉ ላሉ የተለያዩ ሴክተሮች የሰጠው የብድር ክምችት መጠን ብር 8.53 ቢሊዮን ያህል ሲሆን፤ ይህም ከቀደመው ዓመት በብር 1.7 ቢሊዮን ወይም 24.4 በመቶ ከፍ ያለ ነው፡፡ በዚህም ረገድ የተገኘው ውጤት አመርቂ የሚባል ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የብድር ሀብት ጥራት (Asset Quality) በተመለከተ የነበረውን ውጤት በተበላሸ ብድር መጠን ሲለካ የተመዘገበውን ውጤት ስንመለከት ደግሞ 1.68 በመቶ የነበረ ሲሆን፤ ይህም የተሠጡት ብድሮች ገቢ ከማስገኘት አንፃር ጥሩ እንደነበሩ የሚያሳይ ነው፡፡

በሌላ በኩል ባንኩ በበጀት ዓመቱ ከ›KU ›kõ ¾v”¡ አገልግሎት ዘርፍ  ያገኘው የገቢ መጠን  400.9 ሚሊዮን ሆኖ ሲመዘገብ፤ ይህም መጠን ከባንኩ አጠቃላይ ገቢ 23 በመቶ የሚሆነውን የሸፈነ ነበር፡፡

የባንኩ ጠቅላላ ገቢም ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ25 በመቶ ጨምሯል፡፡ ከግብር በፊት የተመዘገበው የትርፍ መጠንም አምና በተመሳሳይ ወቅት ተመዝግቦ ከነበረው የብር 358.2 ሚሊዮን መጠን በበጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ወደ ብር 428.5 ሚሊዮን ተመነደጓል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በባንኩ የሰው ኃይል እድገት የተመዘገቡትን እንቅስቃሴዎች ስንመለከት ደግሞ እ.ኤ.አ. በሰኔ 30 ቀን 2016 ላይ የባንኩ አጠቃላይ የሰው ኃይል በቁጥር 3,123 የደረሰ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 334 የሚሆኑት በአመራር የስራ መደብ (Managerial) ላይ የሚገኙ ሠራተኞች ሲሆኑ፤ 1,777 የሚሆኑት በፅህፈት የስራ መደብ (Clerical) እንዲሁም 1,102 የሚሆኑት ሠራተኞች ደግሞ ፅህፈት ባልሆነ የሥራ መደብ (Non Clerical) ላይ የሚገኙ ሠራተኞች ናቸው፡፡ የሠራተኞች ቁጥር ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ 289 ሠራተኞች ብልጫ አሳይቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ 438 ሠራተኞች ሲቀጠሩ በተለያዩ ምክንያቶች ከባንኩ ጋር የሥራ ውላቸው የተቋረጠ ሠራተኞች ብዛት 149 ሆኗል፡፡

ከሰውኃይልልማትናአስተዳደር ጋርም በተያያዘ በዚህ ዓመት በተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ላይ ለሚገኙ የባንኩ ሠራተኞቹ ከተለያዩ የማሰልጠኛ ተቋማት ጋር በመተባበር በአገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ አገር ጭምር ሥልጠናዎች የተሰጡ ሲሆን ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ በመካከል ደረጃ ለሚገኙ የሥራ መሪዎች በተለየ ሁኔታ (Personal Development) የአመራር ብቃት ማጐልበቻ ሥልጠናዎችን እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

የሥልጠናውምዋናውግብ በሴክተሩ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል የሰው ኃይል ብቃትና ጥራት ወሳኝ በመሆኑ ይህንን አቅም መገንባት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ባንኩ በፅኑ ስለሚያምን ነው፡፡

 

የተከበራችሁ ባለአክሲዮኖች !

ክቡራትና ክቡራን!

 

 

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት  በባንኩ በሚሠጡ የመልቲ ቻናል የባንክ አገልግሎቶች የደንበኞች የመጠቀም ዝንባሌ በላቀ ሁኔታ ጨምሮ ታይቷል፡፡ በዚህ ረገድ  የባንኩን አገልግሎቶች ዘርፈ ብዙ በሆነ አማራጭ ለደንበኞች ለማድረስ አስቀድመን የሄድንበት አካሄድ ለተመዘገበው ውጤት በምክንያትነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ሕብረት ባንክ በበጀት ዓመቱ ቀላል የማይባል ጊዜና ጉልበት የጠየቁ ሥራዎችን በመሥራትና ባለ ብዙ አማራጭ የአገልግሎት አይነቶችን በመዘርጋት እንዲሁም የቴክኖሎጂ አሠራርን ደጋፊ በማድረግ  ቀጣይነትን መሠረት ያደረገ የአሰራር ሥርዓት ለተጠቃሚዎች በማቅረብ የተወዳዳሪነት ብልጫውን ጠብቆ ቆይቷል፡፡ በኤሌክትሮኒክ የባንክ አገልግሎት በባንኩ የተመዘገበውን የሥራ ውጤት በመመልከት ለመረዳት እንደምንችለውም ባንኩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የአሠራሩ አካል ለማድረግ ያፈሰሰው መዋዕለ ነዋይ በእርግጥም ፍሬ ማፍራት መጀመሩንና ለባንኩም ተጨባጭ የሆኑ ጠቀሜታዎችን መስጠት መጀመራቸውን ነው፡፡

 

በተጠቀሰው በጀት ዓመት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያደር ሲብስበት እንጂ ሲሻሻል ብዙም ያልታየው የውጪ ምንዛሪ እጥረት ለሥራ እንቅስቃሴው የደቀነውን ስጋት ከግምት ውስጥ በማስገባት ባንኩ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተጨማሪ ከሁለት ዓለም አቀፍ የካርድ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ማለትም ከቪዛ ኢንተርናሽናልና ከቻይና ዩኒየን ፔይ ጋር አብሮ መስራት ጀምሯል፡፡ የነዚህ ሁለት ድርጅቶች የባንኩ የሥራ አጋር መሆን፤ በተለይ ለንግድ ተጓዦችና ቱሪስቶች የምናቀርበውን አገልግሎት ምቹና የተቀላጠፈ ለማድረግና የባንካችንን የውጪ ምንዛሪ አቅም በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚያበረክት ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ሃዋላ ያለንን የተጠቃሚነት ድርሻ ለማስፋት በማቀድ ባንኩ ከነበሩት በተጨማሪ ከአዳዲስ ዓለምአቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅት ጋር የሥራ ግንኙነት ፈጥሯል፡፡ ይህም ባንኩ የፋይናንስ አቅሙን ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ ረገድ  አወንታዊ ሚና እንደሚጫውት ዕሙን ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከተጨማሪ የዓለምአቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር ተመሳሳይ የሥራ ግንኙነት መፍጠር የቀጣዮቹ ዓመታት ሥራችን ዋነኛ ትኩረት ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል::

በሌላ በኩል የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎታችንን ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ ለማስተዋወቅና የአገልግሎቱን ተጠቃሚዎች ቁጥር ከፍ ለማድረግ በበርካታ ከተሞች ስለአገልግሎቱ ሰፊ የሆነ የማስተዋወቅ ሥራ የተሠራ ሲሆን፤ደንበኞች በባንኩ የሕብር ኦንላይን ወይም ሕብር ሞባይል አገልግሎቶች በመጠቀም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ድረገጽ ላይ የበረራ ጉዞ ማስያዝ ወይም (Book) በማድረግ ክፍያ የሚፈፅሙበትን አሰራር መጀመሩ በበጀት ዓመቱ በባንኩ ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ ለማከናወን ከቻይናው ግዙፍ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ቻይና ጂያንግሱ ኢንተርናሽናል ግሩፕ ጋር  እ.ኤ.አ. ግንቦት 2015 መፈራረማችን የሚታወስ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎም የሕንፃ ግንባታ ሥራው እየተፋጠነ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ ሕብረት ባንክ አብረውት የግል ባንክ ኢንዱስትሪውን በተቀራረበ የጊዜ ልዩነት ከተቀላቀሉት 6 አቻ የግል ባንኮች መካከል ከሁሉም ዘግይቶ የተመሰረተ ባንክ እንደመሆኑ መጠን በበጀት ዓመቱ በሁሉም ረገድ የተገኘው ውጤት በየትኛውም መስፈርት ቢመዘን አመርቂ መሆኑን መረዳት አይከብድም፡፡

 

የተከበራችሁ ባለአክሲዮኖች 

የተከበራችሁ የዲሪክተሮች ቦርድ አባላት፣

ክቡራትና ክቡራን፣

 

ምንም አንኳን ባንኩ በበጀት ዓመቱ አስቸጋሪና እጅግ ፈታኝ በሆነ የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ ያለፈ ቢሆንም የተመዘገበው ውጤት የባንካችንን ወቅታዊ ጥንካሬ ያሳየና የባለአክሲዮኖቻችንን ጥቅም ከማሳደግ አንፃር አወንታዊ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በአቀረብኩት ዘገባ ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡ በዚህ የእድት ውጤት ላይ በመመርኮዝ እ.ኤ.አ. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ድረስ ሙሉ በሙሉ በተከፈለበት አክሲዮን ላይ የ25 በመቶ የትርፍ ክፍያ እንዲደረግ የዲሪክተሮች ቦርድ የውሳኔ ሐሳቡን አቅርቧል፡፡ ይህንን አስመልክቶ ዝርዝሩ ቦርዱ በአቀረበው ሪዞልሽን ላይ ተመልክቷል፡፡

 

በዚህ አጋጣሚ በባንኩ ቦርድ፣ ሥራ አመራርና ሠራተኞች ስም በእስከአሁኑ የሥራ ሒደት ለተቀዳጀነው ስኬት መሠረት ለሆኑ ደንበኞቻችን አጅግ ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

 

በተመሳሳይ በባንካችን የቦርድ አባላት፣ በባንኩ የሥራ አመራርና ሠራተኞች እንዲሁም በባንኩ ባለአክሲዮኖች መካከል የሰፈነው ውስጣዊ ስምምነት በአርአያነት ምሳሌ ሆኖ የሚቀርብ በመሆኑ አድናቆቴን እየገለፅኩ  ንግግሬን ስቋጭ  በዚህ የተገኛችሁ ሁሉ አብራችሁን በመሆን የሥራ ጊዜያቸውን ላጠናቀቁት የባንኩ የቦርድ አባላት እንዲሁም ለባንኩ የሥራ አመራርና ሠራተኞች ሁሉ ላቅ ያለ ምስጋና እንዳቀርብ እንድታግዙኝ እጠይቃለሁ፡፡  የቀድሞዎቹን በመተካት አዲስ ለተሰየሙት ተተኪ የቦርድ አባላትም ከመቼውም ባለቀ ሁኔታ በአሁኑ ወቅት   እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ‹‹የአገልግሎት ልቀት›› ግብ ከዳር ለማድረስ እንዲቻል ተገቢውን አስተዋፅኦ እንድታደርጉ እጠይቃለሁ፡፡

 ስለአዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡

ሕዳር 08 ቀን 2009 ዓ.ም.

ኅዳር 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በተከናወነ ሥነ-ስርዓት የሕብረት ባንክ ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች የባንኩ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ በሚከናወንበት የፕሮጀክት ቦታ ላይ በመገኘት ግንባታው የደረሰበትን ደረጃ ጎበኙ፡፡

በጉብኝት ፕሮግራም ላይ ከባንኩ ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች በተጨማሪ የባንኩ የዲሪክተሮችና የማኔጅመንት አባላት የተገኙ ሲሆን፤ የባንኩ የዲሪክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ ዛፉ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለፁት ዕለቱ ባንኩ ለደረሰበት የእድገት ደረጃ የኋላ ደጀን በመሆን ትልቅ ድርሻ ከሚወስዱት የባንኩ ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች ጋር አንድ ላይ በመሆን በፍፁም ስምምነት ለአንድ ዓላማ በጋራ በመሰለፍ የተገኘውን የጥረት ፍሬ ወደ ሌላ አዲስ የውጤት ምዕራፍ መሸጋገሩን በጋራ የሚከበርበት ዕለት መሆኑን አውስተዋል፡፡ በተጨማሪም  ከጅምሩ ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በተወጣጡና  ለጋራ ዓላማ  አንድ ላይ በቆሙ ባለአክሲዮኖች የተገነባው ሕብረት ባንክ መለያ የሆነው ሰፊ ማዕቀፍ ያለው የትብብር መንፈስ በባንኩ የዲሪክተሮች ቦርድ፣ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች በሰፊው የሚንፀባረቅ መሆኑን አድናቆት የሚሰጠውና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት የሕንፃው ግንባታ የደረሰበት ደረጃ በመሀል በሚያጋጥሙ የተለያዩ እንቅፋቶች ሳይበገር ፍሬ እንዲያፈራና ሕንፃው በታሰበለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የባንኩ ቦርድ ጠንካራ ድጋፍ እንደማይለይ ገልፀዋል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ህንፃው የደረሰበትን ደረጃ አስመልክቶ በእስክንድር አርኪቴክትስ የአርኪቴክቸራል ኩባንያ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አርኪቴክት እስክንድር ውበቱ ገለፃ የተደረገ ሲሆን፤ በተጨማሪም የፋውንዴሽን ኤክስፐርትና የሕንፃ ግንባታው አማካሪ የሆኑት ኢንጅነር ጌታነህ ተረፈ የሕንፃ ግንባታው አሁን ያለበት ደረጃ እስኪደርስ በተሰሩ ሥራዎች ዙሪያ ዝርዝር ማብራሪያ ሠጥተዋል፡፡ በመጨረሻም የሥነ ሥርዓቱ ታዳሚዎች የሕንፃውን ግንባታ ክንውን በመስክ ጉብኝት  አጠቃለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ዜግነት ባላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ስም የተመዘገቡ የባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አክሲዮኖችን እና የትርፍ ድርሻ ክፍያን አስመልክቶ ባወጣው ጋይድላይን ቁጥር FIS/01/2016 የውጭ ዜግነት ባላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ስም የተመዘገቡ አክሲዮኖች የአክሲዮን ሰርተፊኬቶች ለባንኩ ተመልሰው አክሲዮኖቹ በወጡበት ዋጋ ለባለአክሲዮኖቹ እንዲከፈል የተወሰነ  መሆኑን አሳውቋል፡፡ 

በመሆኑም የሕብረት ባንክ አ.ማ. ባለአክሲዮን የሆናችሁ የውጭ ዜግነት ያላችሁ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ይህ ማስታወቂያ በጋዜጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ባሉት 60 ተከታታይ ቀናት ውስጥ የአክሲዮን ሰርተፊኬት ዋናውን ለባንኩ ፋይናንስና አካውንትስ መምሪያ በመመለስ አክሲዮኖቹ የወጡበትን ዋጋ (Par Value) እና እ.ኤ.አ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ድረስ ያለው የትርፍ ድርሻ ክፍያ  በአካል በመቅረብ ወይም በሕጋዊ ወኪል አማካኝነት እንድትወስዱ እናሳውቃለን፡፡  በተጨማሪም እ.ኤ.አ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ድረስ ያለው የአክሲዮኖቹ የትርፍ ድርሻ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ሕዳር 8 ቀን 2009 ዓ.ም የሚያደርጉት 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ስብሰባ ቃለጉባኤ በሚመለከተው አካል እንደተመዘገበ የሚከፈል መሆኑን  እናሳውቃለን፡፡

 

ሕብረት ባንክ አ.ማ.

This new Branch is integrated to the core banking system of the bank, providing a full-fledged modern banking service.


Mickey Leland Condominium Branch 

Addis Ababa

+251-11-273 08 71

 

በሕብረት ሰርተን በሕብረት እንደግ!

United, we prosper!
www.unitedbank.com.et