ሕብረት ባንክ ከምስረታው ጀምሮ ባለፈባቸው 20 የስኬት ዓመታት የገነባውን ትልቅ አቅም አጠንክሮና ይበልጥ አጎልብቶ ለማስቀጠልና በአሁኑ ወቅት በአገራቸንም ሆነ በአፍሪካና በዓለምአቀፍ ደረጃ በሚታዩ ለእድገት በር ከፋች የሆኑ ኢኮኖሚያዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎች አኳያ ባንኩን በሚፈለገው ደረጃ ወደፊት እንዲጓዝ ለማስቻል የሚያግዘውን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ ተግባራዊ አደረገ፡፡

ፍኖተ ካርታው ሕብረት ባንክን በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ 5 ታላላቅ የባንክ ተቋማት አንዱ የማድረግ ታላቅ ራዕይን ሰንቋል፡፡ ሕብረት ባንክ ይህንን የረዥም ጊዜ ስትራቴጂ እንዲነደፍ ምክንያት ከሆኑ ምክንያቶች መካከልም  ፍኖተ ካርታው  በአሁኑ ወቅት በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ላይ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የገበያ ፉክክር ሰብሮ ለመውጣት እና ከዕለት ዕለት እየጨመረ ያለውን የደንበኞች የማያቋርጥ ፍላጎት በቴክኖሎጂ በተደገፈ ዘመናዊ አሰራር በአጥጋቢ ሁኔታ ለመመለስ እንዲቻል የሚጫወተው ሚና የጎላ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡  በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታዩ ያሉ መልካም የቢዝነስ እድሎችን ለመጠቀም የሚያስችለውን አቅም በማጎልበት በሁሉም ረገድ ተመራጭ ባንክ የሚሆንበትን መንገድ መቀየስ አንዱ ነው፡፡

በዚህ ረገድ ሕብረት ባንክ አቅሙን ለማጎልበት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን የረዥም ጊዜ የስትራቴጂክ እቅድ የመንደፍ ልምድ ካለው ዓለም አቀፍ ኩባንያ ጋር ያደረገው የሥራ ስምምነት ባንኩን ወደተሻለ የእድገት መስመር እንዲገባ በማገዝ እና በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ስምና ዝና አሁን ከሚገኝበት ወደ ላቀ ከፍታ ለመውስድ አይነተኛ እርምጃ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ሕብረት ባንክ ስትራቴጂውን ለመንደፍ የሚቸል ኩባንያ ለመምረጥ ዓለም አቀፍ አማካሪ ኩባንያዎችን ያሳተፈ ዓለምአቀፍ የጨረታ ሒደትን የተከተለ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱን አሸናፊ ለሆነው በዓለም  ካሉት አራት ታላላቅ አማካሪ ኩባንያዎቸ አንዱ ለሆነው ዲሎይት እ.ኤ.አ. በሚያዚያ 2018 ሰጥቷል። የባንኩን ስትራቴጂዊ አካሄድ እና የቢዝነስ ሞዴል በማሻሻል በባንኩ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ Transformational Change ለማምጣት በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ በዚህም መሠረት የባንኩ ራዕይ፣ ተልዕኮ እና እሴቶች ለውጡኑ ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንደ አዲስ ዳግም ተቀርፀዋል፡፡

ፍኖተ ካርታው በየደረጃው በባንኩ ማነጅመንትና ዲሬክተሮቸ ቦርድ አባላት ውይይት ተደርጎበት የዳበረ  ሲሆን፣በመጨረሻም የባንኩ የዲሪክተሮች ቦርድ ያፀደቀው ነው፤ ይህንን ተከትሎም የስትራቴጂው ቀጣይ ምዕራፍ የሆነው የትግበራ ሒደት ይፋ ተደርጓል፡፡ ይህ 2030 (እ.ኤ.አ) .ፍኖተ ካርታ ባንኩን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡ 

ስለ ሕብረት ባንክ

ሕብረት ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ባለው ጠንካራ የፋይናንስ አቅም፣ በሕዝብ ዘንድ ባዳበረው አመኔታና የላቀ ዝና በግንባር ቀደምነት ስማቸው ከሚጠቀሱ ጥቂት የግል ባንኮች ተርታ የሚመደብ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የተሰራጩ ከ244 በላይ ቅርንጫፎች በመክፈት ዘርፈ ብዙ የሆኑ የባንክ አገልግሎቶች የሚሠጥ ትልቅ የባንክ ተቋም ነው፡፡

ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶችን ለአገራችን በማስተዋወቅ ፈርቀዳጅ የሆነው ሕብረት ባንክ በግንባር ቀደምነት ለአገራችን የባንክ ዘርፍ ካስተዋወቃቸው ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች መካከል የኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት፣ የኤስኤምኤስ የባንክ አገልግሎትና የስልክ የባንክ አገልግሎቶች በዋነኝነት የሚጠቀሱ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም በላቀ የቴክኖሎጂ ውጤት በመደገፍ ዘርፈ ብዙ የባንክ አገልግሎቶችን ለተጠቃሚዎች ያቀርባል፡፡ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከልም የሕብር የኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት፣ የሕብር የሞባይል የባንክ አገልግሎት፣ የሕብር የወኪል የባንክ አገልግሎት፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትና ሌሎችም የመልቲ ቻናል የባንክ አገልግሎቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ ሌሎችም ዘርፈ ብዙ የሆኑ መደበኛ የባንክ አገልግሎቶችን ለደንበኞች ያቀርባል፡፡