ባለው የካፒታል አቅም 'የሰለጠነ የሰው ኃይል የቅርንጫፍ ስርጭት የገበያ ድርሻና የትርፋማነት ደረጃ በአሁኑ ወቅት በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ከሆኑ ትልልቅ የአገራችን የባንክ ተቋማት ተርታ አንዱ የሆነው ሕብረት ባንክ አ.ማ. በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ሠንጋ ተራ እየተባለ በሚጠራው ሥፍራ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የንግድ ሥራ ኮሌጅ ፊት ለፊት ለሚያስገነባው የባለ 32 ፎቅ እጅግ ዘመናዊና ለትውልድ ተሻጋሪ የሆነ ሕንፃ የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ ሥርዓት ታዋቂው አትሌት ክቡር ዶ/ር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴን ጨምሮ የባንኩ የዲሪክተሮችና የአመራር አባላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ግንቦት 21 ቀን 2006 ዓ.ም. በደማቅ ሁኔታ ተከናወነ፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ ዲበኩሉ እንደተናገሩት ሕብረት ባንክ ከዕለት ዕለት በሁሉም ረገድ እያደገና ተጨባጭ በሆኑ የለውጥ ማሳያዎች አቅሙን በከፍተኛ ሁኔታ እያዳበረ የመጣ ባንክ እንደመሆኑ መጠን የራሱን የዋና መ/ቤት ሕንፃ ማስገንባቱ ባንኩ በሕብረተሰቡ ዘንድ የገነባውን መልካም ስምና ዝና ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያሸጋግር ለማስቻል አይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ እንደ አቶ ታዩ ገለፃ ባንኩ ለሚያሰገነባው የባለ አራት ደርዝ የምድር ውስጥ የመኪና ማቆሚያና የ32 ፎቅ ከፍታ ያለው የዋና መ/ቤት ሕንፃ የሚያስፈልገውን ስፍራ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ከተረከበበት ዕለት ጀምሮ በርካታ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ የሕንፃውን ዲዛይን ውድድር ባሸነፈው በእስክንድር ውበቱና ተባባዎቹ አማካ በኩል የተሰራወን የሕንፃውን ዲዛይን ሦስት ምዕራፍ ባቀፈ ቅደም ተከተል ለማጠናቀቅ የስኬማቲክ (Schematic) እና ፕሪሊሚነሪ (Preliminary) ዲዛይን የባንኩ የዲሪክተሮች ቦርድ አባላትን ጨምሮ የሕንፃውን ዲዛይን በተመለከተ ምክር የሚሰጡ ባለሙያዎችንና ሪቪዎርስን ባሳተፈ ሂደት ማፅደቁን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ሕንፃው በሚገነባበት ስፍራ የአፈር ምርመራና ሌሎች ተገቢ ጥናቶችና ምርመራዎች ተደርገው በመጠናቀቃቸው የመሠረት ማዕቀፊያ (Shoring) ዲዛይን እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የመሠረት ድንጋዩን ያስቀመጠው የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር ዶ/ር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ በበኩሉ ባንኩ በግሉ ሴክተር የተሠማሩ ባለሃብቶችን በመደገፍ ከሚያደርገው ዘርፈ ብዙ ጥረት በስተጀርባ አቅሙን በከፍተኛ ሁኔታ እየሰፋና እያሳደገ የመጣ ባንክ እንደመሆኑ መጠን የራሱን የዋና መ/ቤት ሕንፃ መገንባቱ የሚጠበቅና አስፈላጊም ጭምር እንደሆነ ገልጧል፡፡