ሕብረት ባንክ አ.ማ. ታህሳስ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ባከናወነው ‹‹የወጪ ንግድ ደንበኞች ቀን›› ላይ በወጪ ንግድ ዘርፍ ከባንኩ ጋር ለሠሩና አይነተኛ ሚና ለተጫወቱ ደንበኞቹ የዋንጫና የምስክር ወረቀት ሽልማት ሰጠ፡፡

በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ ዲበኩሉ እንደገለፁት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በወጪ ንግድ ዘርፍ አገራችን ያስመዘገበችው እድገት ከዘርፉ የሚገኘውን የውጪ ምንዛሪ ገቢን በማሳደግና በኢኮኖሚ ውስጥ መነቃቃትን በመፍጠር እየተመዘገበ ላለው የኢኮኖሚ እድገት ግብዓት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ አያይዘውም በዚህ ረገድ አገራችን ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ እንድታሳድግ በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ የዘርፉ ተሳታፊዎች ሚና እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው እንደ ባንክ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ በዚህ ረገድ የሚገኘውን ውጤታማነትን በመወሰን ረገድም ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አስታውሰዋል፡፡ 

በሥነሥርዓቱ ላይ እንደተገለፀው የዝግጅቱ ዓላማም በወጪ ንግድ ከሕብረት ባንክ ጋር አብሮ በመስራት ለባንኩ በውጭ ምንዛሪ ግኝት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ደንበኞችን የተግባር ድምቀታቸውን በእውቅናና በሽልማት ለማወደስ ብሎም በባንኩና በደንበኞቹ መካከል ያለውን የጋራ መደጋገፍ አጠንክሮ ለመዝለቅ ታስቦ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ሕብረት ባንክ እ.ኤ.አ. በሰኔ 30 ቀን 2014 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ለወጪ ንግድ ዘርፍ ብቻ ከ888 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር የሰጠ ሲሆን፤ በሽልማት ሥነስርዓቱ ላይ በአሁኑ ወቅት በአገራችን በወጪ ንግድ ዘርፍ ውስጥ የጎላ ሚና ያላቸው ስመ ጥር የዘርፉ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ በዝግጅቱ ላይ በተለያያ ዘርፍ በመሰማራት ለባንኩ ከፍተኛ ገቢ ላስገቡ 22 ደንበኞች የዋንጫና ሠርተፍኬት ሽልማት የተሰጠ ሲሆን፤ በተመሳሳይ 41 ለሚሆኑ ደንበኞች የሰርተፍኬት ሽልማት ተሰጥቷል፡፡