Print 

እሁድ ጥር 3 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም በእቴጌ ጣይቱ ሆቴል ቅጥር ግቢ ውስጥ ሚገኘው እቴጌ ጣይቱ ቅርንጫፋችን ላይ ባጋጠመን ድንገተኛ የእሳት አደጋ ምክንያት የደረሰውን ጉዳት ለመግለጽና ደንበኞችንም ከስጋት ነፃ እንዲሆኑ ግንዛቤ ለመስጠት የተሠጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

በዕለቱ በተከሰተዉ የእሣት አደጋ የአዲስ አበባ የእሣትና ድንገተኛ አደጋ መከላከል፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ እንዲሁም የአካባቢው ህብረተሰብ ላደረጉልን እገዛና ትብብር ከፍተኛ ምሥጋናችንን እናቀርባለን፡፡

በተጨማሪም የሚዲያው ማህበረሰብ በተለይም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ፣ የሸገር 1ዐ2.1፣ ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት እና ሌሎችም በዕለቱ በቦታው በመገኘት ተገቢውን መረጃ ለአገልግሎታችን ተጠቃሚና ለማህበረሠቡ በማድረሳችሁ ከፍተኛ ምሥጋናችንን እናቀርባለን፡፡

እንደሚታወቀው ባንኩ ለረጅም ዓመታት የኮር ባንኪንግ ስርአትን በመጠቀም ያለምንም እንከን በሺዎች ለሚቆጠሩ በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ ደንበኞቹ አገልግሎቱን ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፤ አሁን ባጋጠመው ድንገተኛ አደጋ የእቴጌ ጣይቱ ቅርንጫፋችን ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎቱ የሚቋረጥ ቢሆንም ደንበኞች ሌሎቹን 107 ቅርንጫፎቻችንን በአማራጭነት መጠቀም የሚችሉ መሆኑን እናረጋግጥላችኋለን፡፡

ባንካችን እ.ኤ.አ. ከ2ዐዐ6 ጀምሮ ሁሉንም ቅርንጫፎቹን በመረጃ መረብ ያስተሳሰረ ሲሆን በቅርቡም ይህን አገልግሎት ወደላቀ የቴክኖሎጂ አቅም ማለትም በዓለም ታዋቂ የሆኑት  ሲቲ ባንክን የመሳሰሉ ባንኮች ወደሚገለገሉበት ፍሌክስ ኪዊብ 12.ዐ1 ቨርዥን ከአመት በፊት በማሳደግ ለደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡  ይህም በመሆኑ እሳት አደጋ የደረሰበት የእቴጌ ጣይቱ ቅርንጫፋችን ደንበኞች የሂሣብ መረጃ ሙሉ በሙሉ ዋናዉ መስሪያቤት በሚገኝ በመረጃ ቋታችን (data center) ያለ በመሆኑ በአገልግሎታችን ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተፅዕኖ አያደርስም፤ ደንበኞቻችንም ቅርንጫፎቻችንን ጨምሮ በሌሎቹም የአገልግሎት መስጫ መንገዶቻችን ማለትም በሞባይል፣ በኢንተርኔት፣ በኤቲኤም እና በሌሎቹም የተለመደዉን ጥራት ያለዉ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን እናሳውቃለን፡፡ እሳት ያልበገረውን ካዝና በግራይንደር በመቁረጥ ገንዘቡ ወጥቶ ተቆጥሮ ከመዝገብ ጋር ተመሳክሮ ትክክለኛነቱ ተረጋግጧል፡፡  ከዚህ በተጨማሪ ቅርንጫፉ ሲገለገልባቸዉ የነበሩ ንብረቶች በሙሉ ኢንሹራንስ ቀድሞ የተገባላቸው በመሆኑ ይህ ጉዳት አሳዛኝ ቢሆንም ንብረቶቹ በቅርቡ የሚተኩ መሆኑን እየገለፅን፤ በእዚህ አጋጣሚ ውድ ደንበኞቻችንና ከጐናችን የቆማችሁ ሁሉ ለሰጣችሁን ድጋፍ እጅግ እናመሰግናለን፡፡

 ደንበኞቻችን ለሚኖራችሁ ተያያዥ ጥያቄዎች የቅርንጫፉን ስራ አስኪያጅ በስልክ ቁጥር 0911636522 ማግኘት የምትችሉ መሆኑን በትህትና እንገልጻልን፡፡

 

ሕብረት ባንክ አ.ማ.

                                                                                                         ጥር 4 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም.