ሕብረት ባንክ አ.ማ. ከባንኩ ጋር በወጪ ንግድ ዘርፍ አብሮ በመስራት ለባንኩ ውጤት ማማር አይነተኛ ሚና ለተጫወቱ ደንበኞቹ የዋንጫና የምስክር ወረቀት ሽልማት ሠጠ፡፡

ታኅሣሥ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል በተደረገው የባንኩ ‹‹የወጪ ደንበኞች ቀን›› ላይ  ንግግር ያደረጉት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ ዲበኩሉ እንደገለፁት በአገር አቀፍ ደረጃ ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በጥራት፣ በተወዳዳሪ ዋጋና በሚፈለገው መጠን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት አሁንም ዘርፈ ብዙ በሆኑ ችግሮች ሳቢያ ፈታኝ መሆኑ እንደቀጠለ መሆኑን አውስተዋል፡፡ አያይዘው እንደተናገሩትም በችግሮች ሳይበገሩና በፈተናዎች ሳይረቱ በወጪ ንግድ ተሰማርተው ከባንኩ ጋር በመሥራት ለባንኩ ውጤት አወንታዊ ሚዛን የሚደፋ ሥራ ላበረከቱ ደንበኞች ያላቸውን አክብሮት በመግለፅ እ.ኤ.አ. ከሐምሌ 2015 ጀምሮ ለተከታታይ 15 ወራት ለባንኩ ውጤት ማማር በወጪ ንግድ ዘርፍ የጎላ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ደንበኞች እውቅና ለመስጠት የዋንጫና የእውቅና የምስክር ወረቀት ሽልማት እንደተዘጋጀ ገልፀዋል፡፡

እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ በዘርፉ ተሰማርተው ያሉ የላኪዎችን የፋይናንስ ፍላጎት በአጥጋቢ ሁኔታ ለማሟላት የባንኮች ሚና የላቀ በመሆኑ ሕብረት ባንክ አ.ማ. ባለው ጠንካራ የፋይናንስ አቅምና እጅግ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ግብዓት በመታገዝ ወቅቱ የሚጠይቀውን ዘመናዊና እጅግ ቀልጣፋ አሰራር በዘርፉ ለተሰማሩ ደንበኞቹ እያቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአገሪቱ ውስጥ እየታየ ያለውን ሥር የሰደደ የውጪ ምንዛሪ እጥረት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ባንኩ በወጪ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ደንበኞቹ ተወዳዳሪ የሆኑ የአገልግሎት አይነቶችን በማቅረብ ረገድ ብርቱ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 ሕብረት ባንክ አ.ማ. ባዘጋጀው የወጪ ንግድ ደንበኞች ቀን ሥነ-ስርዓት ላይ በአሁኑ ወቅት በአገራችን በወጪ ንግድ ዘርፍ ከፍተኛ ገቢ በማስገባት አይነተኛ ሚና በመጫወት ላይ ካሉ ስመ ጥር የዘርፉ ተሳታፊዎች መካከል ባካበቱት ጠንካራ የሥራ ልምድና በገነቡት መልካም ስምና ዝና አንቱታን ያተረፉ አስመጪና ላኪ ድርጅቶች የተገኙ ሲሆን፤ በተለያየ ዘርፍ በመሰማራት ለባንኩ ከፍተኛ ገቢ ላስገቡ 15 ደንበኞች የዋንጫና የሠርተፍኬት ሽልማት ሲሰጥ በተመሳሳይ 36 ለሚሆኑ ደንበኞች የሠርተፍኬት ሽልማት ተሠጥቷል፡፡ እንደዚሁም በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ለባንኩ የውጭ ምንዛሪ በማስገኝት ላበረከቱት አስተዋፅኦ  የእውቅና ሰርተፊኬት ተሠጥቷል፡፡

ስለ ሕብረት ባንክ አ.ማ.

ሕብረት ባንክ አ.ማ. በአገራችን የግል ባንክ ዘርፍ ባለው የካፒታል አቅም በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ከሆኑ ትልልቅ የአገራችን የባንክ ተቋማት ተርታ የሚሰለፍ ዘመናዊና ትልቅ የባንክ ተቋም ነው፡፡

ሕብረት ባንክ በአገልግሎት በቆየባቸው ያለፉት 18 ዓመታት በግንባር ቀደምነት ለአገራችን የባንክ ዘርፍ ካስተዋወቃቸው ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች መካከል የኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት፣ የኤስኤምኤስ የባንክ አገልግሎትና የስልክ የባንክ አገልግሎቶች በዋነኝነት የሚጠቀሱ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም በላቀ የቴክኖሎጂ ውጤት በመደገፍ ዘርፈ ብዙ የባንክ አገልግሎቶችን ለተጠቃሚዎች ያቀርባል፡፡ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከልም የሕብር የኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት፣ የሕብር የሞባይል የባንክ አገልግሎት፣ የሕብር የወኪል የባንክ አገልግሎት፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትና ሌሎችም የመልቲ ቻናል የባንክ አገልግሎቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ ሌሎችም ዘርፈ ብዙ የሆኑ መደበኛ የባንክ አገልግሎቶችን ለደንበኞች ያቀርባል፡፡ 

 ባንኩ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን እ.ኤ.አ. በሰኔ 30 ቀን 2016 የባንኩ ጠቅላላ ሀብት ብር 17.3 ቢሊዮን ሆኖ ሲመዘገብ የባንኩ ጠቅላላ ካፒታል 2.07 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ ሕብረት ባንክ ባለፉት 18 ዓመታት ለበርካታ ኢትዮጵያዊያን የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ. በ2015/16 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ከ3200 የሚልቁ ዜጎች በባንኩ ውስጥ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡