ኅዳር 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በተከናወነ ሥነ-ስርዓት የሕብረት ባንክ ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች የባንኩ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ በሚከናወንበት የፕሮጀክት ቦታ ላይ በመገኘት ግንባታው የደረሰበትን ደረጃ ጎበኙ፡፡

በጉብኝት ፕሮግራም ላይ ከባንኩ ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች በተጨማሪ የባንኩ የዲሪክተሮችና የማኔጅመንት አባላት የተገኙ ሲሆን፤ የባንኩ የዲሪክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ ዛፉ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለፁት ዕለቱ ባንኩ ለደረሰበት የእድገት ደረጃ የኋላ ደጀን በመሆን ትልቅ ድርሻ ከሚወስዱት የባንኩ ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች ጋር አንድ ላይ በመሆን በፍፁም ስምምነት ለአንድ ዓላማ በጋራ በመሰለፍ የተገኘውን የጥረት ፍሬ ወደ ሌላ አዲስ የውጤት ምዕራፍ መሸጋገሩን በጋራ የሚከበርበት ዕለት መሆኑን አውስተዋል፡፡ በተጨማሪም  ከጅምሩ ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በተወጣጡና  ለጋራ ዓላማ  አንድ ላይ በቆሙ ባለአክሲዮኖች የተገነባው ሕብረት ባንክ መለያ የሆነው ሰፊ ማዕቀፍ ያለው የትብብር መንፈስ በባንኩ የዲሪክተሮች ቦርድ፣ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች በሰፊው የሚንፀባረቅ መሆኑን አድናቆት የሚሰጠውና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት የሕንፃው ግንባታ የደረሰበት ደረጃ በመሀል በሚያጋጥሙ የተለያዩ እንቅፋቶች ሳይበገር ፍሬ እንዲያፈራና ሕንፃው በታሰበለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የባንኩ ቦርድ ጠንካራ ድጋፍ እንደማይለይ ገልፀዋል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ህንፃው የደረሰበትን ደረጃ አስመልክቶ በእስክንድር አርኪቴክትስ የአርኪቴክቸራል ኩባንያ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አርኪቴክት እስክንድር ውበቱ ገለፃ የተደረገ ሲሆን፤ በተጨማሪም የፋውንዴሽን ኤክስፐርትና የሕንፃ ግንባታው አማካሪ የሆኑት ኢንጅነር ጌታነህ ተረፈ የሕንፃ ግንባታው አሁን ያለበት ደረጃ እስኪደርስ በተሰሩ ሥራዎች ዙሪያ ዝርዝር ማብራሪያ ሠጥተዋል፡፡ በመጨረሻም የሥነ ሥርዓቱ ታዳሚዎች የሕንፃውን ግንባታ ክንውን በመስክ ጉብኝት  አጠቃለዋል፡፡