ሕብረት ባንክ በፍጥነት እያደገ ካለው የቴክኖሎጂ ዓለም ጋር አብሮ ለመራመድ ወቅቱ ከሚጠይቀው የላቀ አሰራር ጋር ራሱን አዋህዶ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ፈር ቀዳጅ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት በመስጠት ይታወቃል፡፡ ለአገራችን የባንክ ኢንዱስትሪ በግንባር ቀደምነት ካስታዋወቅናቸው አገልግሎቶች መካከልም ኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት፣ የሞባይል ባንክ አገልግሎት እና የካርድ ባንኪንግ አገልግሎቶች ይጠቀሳሉ፡፡

1. ሕብር ኦንላይን የባንክ አገልግሎት

ሕብረት ባንክ የኢንተርኔት የባንክ አገልግሎቱን አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አሻሽሎ ሕብር ኦንላይን በሚል ስያሜ መስጠት የጀመረ ሲሆን፤ በዚህ አዲስ አገልግሎት ደንበኞች የሚፈልጉትን የባንክ መረጃ ከማየት ባለፈ ሒሳባቸውን የሚያንቀሳቅሱበት አሰራር የያዘ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ደንበኞች ኢንተርኔት በሚያገኙበት በየትኛውም ስፍራ ለ24 ሰዓታት በሳምንት ለ7 ቀናት https://www.unitedib.com.et ድረ ገፅን በመጠቀም አገልግሎቱን መጠቀም ይችላሉ፡፡
የሕብር ኦንላይን አገልግሎትን በመጠቀም ከሚያገኟቸው አገልግሎቶች መካከል የሚከተሉት በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፤
 • ገንዘብ ወደራስዎም ሆነ ወደ ሌላ የሕብረት ባንክ ሒሳብ መላክ
 • የአገር ውስጥ ሃዋላ ማከናወን
 • የግብይት መግለጫ ማግኘት
 • የደመወዝ ክፍያን ጨምሮ ሌሎች ጥቅል የክፍያ አገልግሎቶችን ማከናወንና# ሌሎችም በርካታ አገልግሎቶች፡፡

2. ሕብር ሞባይል የባንክ አገልግሎት

የሕብር ሞባይል የባንክ አገልግሎታችንን በየትኛውም ስፍራ ሆነው ጊዜ ሳይገድብዎ የተንቀሳቃሽ ስልክዎን በመጠቀም እና ባንኩ ከዘረጋው የመረጃ ስርዓት ጋር በማገናኘት የተለያዩ መረጃዎችን ማግኘት እና ሂሳብዎን ማንቀሳቀስ የሚያስችልዎ አሰራር የያዘ አገልግሎት ነው፡፡
አገልግሎቱን ለማግኘት ሒሳብ ወደ ከፈቱበት ቅርንጫፍ በመሄድ ለአገልግሎቱ በመመዝገብ የይለፍ ቁጥር ያገኛሉ ከዛም *811# ላይ በመደወል የሚከተሉትን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን ያገኛሉ፡-
 • ገንዘብ ከራስዎ ሒሳብ ወደሌላ ሰው ሒሳብ ማስተላለፍ፣
 • የባንክ ሂሳብዎን አጠቃላይ መረጃ ማየትና ሂሳብዎን ማንቀሳቀስ፣
 • የብድር ሂሳብዎን ዝርዝር ሁኔታ ማወቅ እና የብድር ክፍያ ጊዜ ማስታወሻ ማግኘት፣
 • አነስተኛ የባንክ ሂሳብ መግለጫዎችን (Mini Bank Statement) ማግኘት፣
 • የየዕለቱን የውጭ አገር ገንዘቦች ምንዛሬ መጠን ማወቅ እና ሌሎችም አገልግሎቶች፡፡

3. ሕብር ካርድ የባንክ አገልግሎት

የሕብር ካርድ የባንክ አገልግሎት ሕብረት ባንክን ጨምሮ በአዋሽና በንብ ኢንተርናሽናል ባንኮች ጥምረት በተቋቋመውና ፕሪሚየም ስዊች ሶልሽንስ ተብሎ በሚጠራው ድርጅት አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ በጣም አዋጭና ለተጠቃሚዎች እጅግ በተመቸ መልኩ የካርድ የባንክ አገልግሎትን በተወዳዳሪዎች መካከል በሚሰጥ የጥምረት አገልግሎት ማቅረብ ያስቻለ አሰራር ነው፡፡ በዚህ መሰረት በፕሪሚየም ስዊች ሶልሽንስ ጥምረት ስር በታቀፉት ስድስት ባንኮች እንዲሁም በቅርቡ በተቋቋመው በኢትዮፔይ የስዊች አገልግሎት በመጠቀም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤቲኤሞችን ጨምሮ በሁሉም ባንክ ኤቲኤሞችን በመጠቀም በሕብር ካርድ መገልገል ይቻላል፡-
በሕብር ካርድ ከሚያገኟቸው አገልግሎቶች መካከል
 • ገንዘብ ማውጣት
 • ቀሪ ሒሳብዎን ማወቅ
 • አጭር የሒሳብ መግለጫ ማግኘት
 • ገንዘብ ማስተላለፍ&
 • ገንዘብ መላክና መቀበል ይጠቀሳሉ፡፡
በተጨማሪም በሕብረት ባንክ ብቻ የተተከሉ የኤቲኤም ማሽኖችን ብቻ በመጠቀም ካለ ተጨማሪ የሰው እርዳታ የአገር ውስጥ ሃዋላ ማከናወን የሚቻል ሲሆን፤ በዚህ መልኩ የተላከን ገንዘብ ከኤቲኤም ለማውጣት የባንክ ሒሳብ መክፈትም ሆነ የሕብር ካርድን መያዝ አያስፈልግም፡፡
ሕብር ካርድን በመጠቀም ሕብረት ባንክን ጨምሮ ከላይ በተጠቀሱት ባንኮች አማካኝነት በተተከሉ የሽያጭ መዳረሻ ማሽኖች (POS Terminals) ላይ ለሚፈጽሙት ግዢና ለሚያገኙት አገልግሎት ከፍያ መፈፀም ሌላው በሕብር ካርድ ማግኘት የሚችሉት አገልግሎት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባንኩ የቪዛ፣ ማስተር ካርድ እና ቻይና ዩኒያን ፔይ አለም አቀፍ ካርዶችን በሁሉም የባንኩ ቅርንጫፎች፣ በኤ.ቲ.ኤም እና ፖስ ማሽኖች ይቀበላል፡፡