ሕብረት ባንክ ስፖንሰር ያደረገው የኢትዮ-አሜሪካ የንግድ ም/ቤት ውይይት ተካሄደ

ሕብረት ባንክ በአጋርነት ስፖንሰር ያደረገው በኢትዮ- አሜሪካ እና በዱባይ የንግድ ም/ቤቶች ትብብር የተዘጋጀው የትውውቅና የውይይት መድረክ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ተጋባዥ እንግዶች፣የሕብረት ባንክ የሥራ ሃላፊዎችና ፣ የኢትዮ-አሜሪካ የንግድ ም/ቤት አባላት በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

ውይይቱ የኢትዮ-አሜሪካ የንግድ ም/ቤት በኢትዮጵያ ውስጥ በንግዱ ዘርፍ እያከናወነ ስላለውና ሊያከናውናቸው ስላቀዳቸው ስራዎች እንዲሁም በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ የሚታዩ ክፍቶችን ለመሙላት በሚያስችሉ ጉዳዩች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡

ሕብረት ባንክ የኢትዮ-አሜሪካ የንግድ ም/ቤት የውይይትና የትውወቅ መድረክን ስፖንሰር በማድረጉ ኩራት እንደተሰማውና እንዲህ ያሉ አጋርነትን የሚያጐለብቱ መድረኮች ለሀገራችን የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ሕብረት ባንክን ወክለው የተገኙት የባንኩ የደንበኞች ተሞክሮ እና ኮርፓሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ሕይወት ዓለማየሁ የገለጹ ሲሆን አክለውም ሕብረት ባንክ ለንግድ ም/ቤቱ አባላት አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዩ-አሜሪካ የንግድ ም/ቤት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኤልያስ ወልዱ በበኩላቸው በአሜሪካን ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢኮኖሚ፣ በማሕበራዊ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለማስተሳስር የሚያግዙ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የንግድ ም/ቤቱ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የኢትዩ-አሜሪካ የንግድ ም/ቤት እና የአዲስ አበባ የዘርፍ እና ንግድ ማሕበራት ምክር ቤት በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡ ሕብረት ባንክ ከዚህ ቀደም ከአዲስ አበባ የዘርፍ እና የንግድ ማሕበራት ምክር ቤት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ፈርሞ በአጋርነት እየሰራ መሆኑ ይታወሳል፡፡

በውይይት መድረኩ ጥናታዊ ፅፎችና በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ስላሉ መልካም አጋጣሚዎች እንዲሁም ለሚታዩ ተግደሮቶች የመፍትሔ ሀሳቦች ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

በሕብረት እንደግ!
ሕብረት ባንክ

Similar Posts