ሕብረት ባንክ ስፖንሰር ያደረገው 4ኛው ዙር የዘለላ ፕሮጀክት የምክክር መድረክ ተከናወነ

ሕብረት ባንክ ከኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሞ ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን በማበረታታት ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ተቀርጾ እየተተገበረ የሚገኘው ’’ዘለላ’’ ፕሮጀክት ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን ለመደገፍና ለማበረታታት ያለመ ፕሮጀክት ሲሆን የስራ ፈጣሪ ወጣቶች የፋይናንስ አቅርቦት ላይ ያተኮረው የፕሮጀክቱ 4ኛ ዙር የምክክር መድረክ ታህሳስ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በሳይንስ ሙዚየም ተከናወኗል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፤ የማስተር ካርድ ፍውንዴሽን እና የሕብረት ባንክ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ስራ ፈጣሪ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ፕሬዚደንት ወ/ሪት ሳሚያ አብዱልቃድር ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት ድጋፍ ያደረጉትን አካላት አመስግነው በተለይም ሕብረት ባንክ በራሱ ተነሳሽነት ወደ ማህበሩ ቀርቦ ወጣቶችን ለመደገፍ ያሳየው ቁርጠኝነት ለሌሎች ባንኮች አርአያ የሚሆን ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሕብረት ባንክ ስትራቴጂና ቴክኖሎጂ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አንዷለም ኃይሉ በበኩላቸው ለስልታዊ አጋርነት /strategic partnership/ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው ሕብረት ባንክ በዘለላ ፕሮጀክት ላይ በአጋርነት በመሳተፉ ኩራት እንደሚሰማው ገልጸው ወደፊትም ባንኩ ከስራ ፈጣሪ ወጣቶች ጎን እንደሚቆም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ከምክክር መድረኩ ጋር ተያይዞ ከታህሳስ 13 እስከ 22/2015 ዓ/ም የሚቆይ የስራ ፈጠራ ኤግዚቢሽን በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀ ሲሆን ወጣቶች የፈጠራ ስራዎቻቸውን እንደሚያስተዋዉቁበት ይጠበቃል፡፡

ሕብረት ባንክ

Similar Posts