ሕብረት ባንክ ከኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ጋር በመተባበር በኢትዮጵያውያን ስራ ፈጣሪዎች እና በቻይና ኩባንያዎች መካከል የንግድ ትስስር መድረክ አከናወነ፡፡

ሕብረት ባንክ ስፖንሰር ያደረገው ይሕ የንግድ ትስስር መድረክ ግንቦት 06 ቀን 2016 ዓ/ም በሕብረት ባንክ መሰብሰቢያ አዳራሽ የተከናወነ ሲሆን የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ከቻይና ኩባንያዎች ጋር የንግድ ትስስር እንዲፈጥሩና ልምድ እንዲለዋወጡ ለማስቻል ያለመ ነው፡፡

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሕብረት ባንክ ስትራቴጂና ቴክኖሎጂ ም/ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አንዷለም ሀይሉ ሕብረት ባንክ አጋርነትን በስትራቴጂው አካቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው በተለይም ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን ለመደገፍ ከሁሉም ባንኮች አስቀድሞ ከኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም አበረታች ተግባር እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምዕራብ፣ የኤዥያ እና የፓስፊክ ሀገራት ዳይሬክተር ጀነራል ዶ/ር ገበየሁ ጋንጋ በበኩላቸው መድረኩ ከንግድ ትስስር እና ልምድ ልውውጥ ባለፈ የኢትዮጵያንና የቻይናን ግንኙነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ፕሬዚደንት ሳሚያ አብዱልቃድር ሕብረት ባንክ ለማህበሩ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀው ማሕበሩ ከኢትዮጵያ አልፎ አለምዓቀፍ ተሞክሮዎችን እያገኘ የወጣት ስራ ፈጣሪዎችን ችግር ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የቻይና-አፍሪካ የወጣቶች ፈጠራ እና ኢንተርፕረነርሺፕ ዳይሬክተር ሺያዎ ሺ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር በቻይና የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አድንቀው ትስስሩን ለማጎልበት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ለቢዝነስ ትስስሩ በመንግስት በኩል ሙሉ ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡

የንግድ ትስስር መድረኩ የመጀመሪያ ዙር ሲሆን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የቻይና ኩባንያዎች፣ የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች፣ የሕብረት ባንክና የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል፡፡

ሕብረት ባንክ

በሕብረት እንደግ!

Similar Posts