ሕብረት ባንክ የካርድ ባንኪንግ አገልግሎቶቹን የማስተዋወቅ ፕሮግራም በይፋ ጀመረ

በሀገራችን ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ግንባር ቀደም ከሆኑ ባንኮች አንዱ የሆነው ሕብረት ባንክ የካርድ ባንኪንግ አገልግሎቶቹን የማስተዋወቅ ፕሮግራሙን በዋናው መስርያ ቤት በተዘጋጀ የመክፈቻ ፕሮግራም መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም አስጀምሯል፡፡

በፕሮግራሙ ማስጀመርያ ወቅት የሕብረት ባንክ የስትራቴጂና ቴክኖሎጂ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አንዷለም ኃይሉ እንደተናገሩት ሕብረት ባንክ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶችን በራስ አቅም በመገንባት የሚታወቅ ሲሆን የባንኩ የኮር ባንኪንግ ስርዓትም በኢትዮጵያ ባልተለመደ መልኩ በራሱ የውስጥ አቅም መገንባቱን ለአብነት አስታውሰዋል፡፡ ሕብረት ባንክ አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ የባንክ አሰራሮችን ዘርግቶ እየሰራ የሚገኝ መሆኑንና የባንኩ የካርድ ባንኪንግ አግልገሎቶችም ዘመናዊና ወቅቱ የሚጠይቀውን የቴክኖሎጂ ደረጃ ያሟሉ፣ ለአያያዝ ምቹ፣ ጊዜና ገንዘብ ቆጣቢ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

አክለውም ደንበኞች ዘመናዊ የሆኑትን የሕብረት ባንክ የካርድ ባንኪንግ አገልግሎቶችን እንዲጠቀሙ ግብዣ አድርገዋል፡፡

ሕብረት ባንክ በአሁኑ ሰዓት ከ9 በላይ የካርድ አይነቶችን በማቅረብ የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን የካርድ ባንኪንግ ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየያደገ መጥቷል፡፡ የደንበኛውን ፍላጎት መሰረት ያደረጉት እንደ ሕብር የግብይት ካርድ፣ ሕብር ሙባህ ካርድ (ለወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች የተዘጋጀ)፣ ሕብር የስጦታ ካርድ፣ ሕብር የደምወዝ ካርድ፣ ሕብር የወጣቶች እና ሕብር የሴቶች ካርድ ለደንበኞች ምቹና ቀልጣፋ አግልግሎት ለመስጠት የተዘጋጁ መሆኑንም በፕሮግራም ማስጀመርያው ወቅት ተጠቅሷል፡፡

ሕብረት ባንክ ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በሕብር ካርዶች በሕብረት ባንክ የኤትኤም ማሽኖች ብቻ ለሚጠቀሙ ደንበኞች ከየትኛውም አይነት የአገልግሎት ክፍያ ነፃ መሆኑን እያበሰረ በሕብረት ካርድና በሕብረት ፖስ ብቻ ለሚገበያዩ ደንበኞች እንዲሁ የግብይቱን 5% ተመላሽ ያደርጋል፡፡

Similar Posts