ሕብረት ባንክ የ2015 ዓ/ም አዲስ አመትን በማስመልከት ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የገንዘብና የኮምፒውተር ድጋፍ አደረገ፡፡

በሕብረት ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ከበደ የተመራው የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች ቡድን ጳጉሜ 03 ቀን 2014 ዓ/ም በመቄዶንያ ተገኝቶ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን በማዕከሉ የሚገኙ አረጋውያንና አዕምሮ ህሙማንን ጠይቀው እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሳላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

በጉብኝቱ ማጠናቀቂያ ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የአምስት መቶ ሺህ (500,000) ብር ቼክ፣ 13 ኮምፒዩተሮች፣ እና አንድ መቶ ጥላዎችን ያስረከቡት የሕብረት ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ከበደ ማዕከሉ የሚያከናውነውን በጎ ተግባር አድንቀው እንደ ሕብረት ባንክ ማዕከሉን በተደራጀ መንገድ የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መስራች የክብር ዶክተር ቢኒያም በለጠ ደጋግ ግለሰቦችና ድርጅቶች የሚያደርጉት ድጋፍ ለማዕከሉ መጠናከር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው ሕብረት ባንክ ላደረገው ድጋፍ በአረጋውያንና በአዕምሮ ህሙማን ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ሕብረት ባንክ በጥር ወር 2014 ዓ/ም ዋና መስሪያ ቤቱን ባስመረቀበት ወቅት ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል 1.5 ሚሊየን ብር ማበርከቱ የሚታወስ ነው፡፡ ሕብረት ባንክ መሰል ተቋማዊ ማህበራዊ ሀላፊነቱን የሚወጣ ባንክ ሲሆን ይህንንም በጐ ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

በሕብረት እንደግ!

Similar Posts